ከእውነት የራቀ›› የአክሲዮን ሽያጭ ማስታወቂያዎች ላይ ቁጥጥር ማድረግ ተጀመረ

 

‹‹ከእውነት የራቀ›› የአክሲዮን ሽያጭ ማስታወቂያዎች ላይ ቁጥጥር ማድረግ ተጀመረ

ቀን: February 11, 2024

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃንና የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣኖች በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እየተበራከቱ የመጡትንና ‹‹ከእውነት የራቁ ማስታወቂዎችን›› እያስነገሩ ያሉ የአክሲዮን ሻጮች ላይ፣ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ መጀመራቸው ታወቀ፡፡

ከተቋቋመ ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን፣ ካሉበት አንደኛውና ዋነኛው ኃላፊነቶቹ ውስጥ ባልተማከለ መንገድ ሲሠራ የነበረውን የአክሲዮን ግዥና ሽያጭ ሒደቶች፣ በሕግ መቆጣጠርና በተማከለ የሕግ ማዕቀፍ ማስኬድ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

‹‹ከእውነት የራቀ›› የአክሲዮን ሽያጭ ማስታወቂያዎች ላይ ቁጥጥር ማድረግ ተጀመረ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና
ዳይሬክተር ብሩክ ታዬ (ዶ/ር)

ምንም እንኳን የአክሲዮን ሽያጮችን በሕግ የመቆጣጠር ሥልጣን ለባለሥልጣኑ ቢሰጠውም፣ በርካታ ዝርዝር የሕግ ማዕቀፎች ዝግጅት ባለማጠናቀቁ፣ በርካታ የአክሲዮን ሽያጮች አማላይ ትርፍ እንደሚያስገኙ በማስነገር ማስታወቂያ እያስተላለፉ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡

– ET Securities Market YouTube-

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በርካታ ድርጅቶች አክሲዮን እንደሚሸጡና ትልልቅ ትርፍ እንደሚያተርፉ ማስታወቂያ የሚያስነግሩ እንዳሉ እየተመለከቱ እንደሆነ ገልጸዋል። በመሥሪያ ቤታቸው ግምገማ መሠረትም፣ ማስታወቂያዎቹ ‹‹ከእውነት የራቁ››፣ እንዲሁም ድርጅቶቹ በሚያስነግሩት ደረጃና የትርፍ ህዳግ መሠረት መክፈል እንደማይቻሉ ነው፡፡

‹‹ሌላ ዓይነት የሒሳብ ቀመር ከሌለ በስተቀር በምንም ዓይነት ሒሳብ ሥሌት መክፈል አይችሉም፤›› ሲሉ ማስታወቂያ የሚየስነግሩበት ሒደት ላይ ያላቸውን ግምገማ ገልጸዋል፡፡ ይህንን አሠራር ለማስቀረትም መመርያውን አጠናቀው እስከሚጨርሱ ድረስ ከመገገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዓይነት ተቋማት ጋር በጋራ እየሠሩ እንደሆነም ብሩክ (ዶ/ር) ተግረዋል፡፡

ሪፖርተር ባደረገው ማጣራትና በተመለከተው የደብዳቤ ልውውጦች መሠረት፣ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ለመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ጥር 23 ቀን 2016 ዓ.ም. በጻፈለት ደብዳቤ ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥቶታል፡፡

የመገናና ብዙኃን ባለሥልጣኑ ጥር 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ለበርካታ መገናኛ ብዙኃን (የድምፅና ቪዲዮ መገናኛ ብዙኃን) በጻፈላቸው ደብዳቤ መሠረት፣ መገናኛ ብዙኃኑ ከዚህ በኋላ አክሲዮን እንዲሸጡ ፈቃድ ላልተሰጣቸው ድርጅቶች ማስታወቂያ እንዳያስተላልፉላቸው ያዛል፡፡

የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን አሁን እያዘጋጀ ያለውን አንድ ዝርዝር መመርያ ሳያጠናቅቅ፣ የአክሲዮን ግዥን ፈቃድ የማይሰጥ ሲሆን፣ ሐምሌ 2013 ዓ.ም. በፀደቀው የካፒታል ገበያ አዋጅ መሠረት ግን ድርጅቶች የኢንቨስትመንት መግለጫ አዘጋጅተው በባለሥልጣኑ ካላስፈቀዱ ማስታወቂያ ማስነገር እንደማይችሉ ይደነግጋል፡፡

የካፒታል ገበያ ባለሥልጣኑም ይህንን ድንጋጌ በማስረዳት ነባር ዝርዝር የሕግ ማዕቀፉን እስኪጠናቅቅ ድረስ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን መገናኛ ብዙኃንን በማዘዝ እንዲተባበረው ጠይቋል፡፡ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣንም ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ላይ ባስተላለፈው ሪፖርተር የተመለከተው ውሳኔ መሠረት፣ መገናኛ ብዙኃን ፈቃድ ሳያዩ ማስታወቂያ ማስተላለፉ ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚያስወስድ ነው ያሳሰበው፡፡

የካፒታል ገበያ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የአክሲዮን ሽያጭን ወደ ተማከለ ሥርዓት ከማስመጣቱ ባሻገር፣ ትልልቅ ሐሳብና ትልልቅ ህልም ይዞ ወደ ገበያ መግባት የሚፈልግ ሰው አሁን ባለው ፋይናንስ የሚገኝበትን የተጣበበ አማራጭ ያሰፋል።

‹‹አንድ ባንክ ላይ ተማምኖና የዚያ ባንክ ይሁንታን ካገኘ ብቻ ነው አንድ ሰው ወደ ሥራ ሊገባ የሚችለው፤›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ብሩክ (ዶ/ር)፣ ‹‹የካፒታል ገበያ ወደ ሙሉ ሥራ ሲገባ ግን በርካታ ትልቅ ህልምና ራዕይ ያለው ሰው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ተማምኖ ወደ ሥራ መግባት ይችላል፤›› ሲሉ አክለው ገልጸዋል።

አስተዳዳሪና ቦርድ ተሶሞለት ሥራ ከጀመረ አንድ ዓመት የሆነው ባለሥልጣኑ፣ የሕግ ማርቀቅን ጨምሮ በአንድ ዓመት ውስጥ በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ እንደነበር ኃላፊው በሚዲያ በሰጡት መግለጫ ላይ አስረድተው ነበር።

ባለሥልጣኑ የዝግጅት ሥራውንም አጠናቅቆ ይፋ እንዳደረገው፣ ከ15 በላይ ለሚሆኑ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ከነገ ሰኞ የካቲት 4 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ፈቃድ መስጠት እንደሚጀምርም ተገልጿል። ከሚሰጡት ፈቃዶች መካከል በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ፈቃድ የሚሰጥበት የኢንቨስትንት ባንክ አንደኛው እንደሆነም ተገልጿል፡፡ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶቹ የሚተዳደሩበት መመርያ በጥር ወር አጋማሽ ላይ ፀድቆ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወቃል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ እንደገለጹት ሦስት የውጭ አገር ኩባንያዎችና ጥቂት የአገር ውስጥ ንግድ ባንኮችን ጨምሮ በርካታ ድርጅቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለማግኘት ፍላጎት እያሳዩ መሆናቸውን ያስረዱ ሲሆን፣ እነዚህ ድርጅቶች የሚኖራቸው ዋነኛ ኃላፊነት ወደ ገበያ የሚመጡ ኩባንያዎችን ማዘጋጀትም ነው፡፡ ለኢንቨስትመንት ባንኮች ፈቃድ የመስጠት ሥልጣኑ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ነው።

ምንጭ:- ሪፖርተር

Please follow and like us:
Pin Share

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Translate »
RSS
Follow by Email
Scroll to Top