ዕጣ የወጣባቸው የ20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሳይጠናቀቁ ለማስተላለፍ ጥናት እየተካሄደ መሆኑ ተነገረ::

www.condoaddis.com

ዕጣ የወጣባቸው የ20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሳይጠናቀቁ ለማስተላለፍ ጥናት እየተካሄደ መሆኑ ተነገረ::

የማጠናቀቂያ ዋጋቸው 19 ቢሊዮን ብር የሚገመትና የግንባታ ደረጃቸው በአማካይ 87 በመቶ የደረሰ፣ ከ29 ሺሕ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን፣ ባሉበት ሁኔታ ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ የሚስችል የዳሰሳ ጥናት እየተካሄደ መሆኑ ታወቀ፡፡

ግንባታቸው ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ በ10/90፣ በ20/80፣ እንዲሁም በ40/60 የቤቶች መርሐ ግብር  ሲገነቡ የቆዩና ግንባታቸው ሙሉ ለሙሉ ያልተጠናቀቀ በተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ፣ እንዲሁም ዕጣ ወጥቶባቸው ያልተላላፉ  በአጠቃላይ 139,000 ቤቶች እንደሚገኙ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ደኤታ አቶ ሔኖስ ወርቁ አስታውቀዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው ይህን የተናገሩት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ጥር 16 ቀን 2014 ዓ.ም. የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የ2014 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ሪፖርት ላይ ግምገማ ሲያደርግ ነው፡፡

ቤቶቹ መሠረታዊ ግንባታ የተጠናቀቀላቸው ቢሆንም፣ ያልተጠናቀቁ መሆናቸውን፣ የውኃ፣ የመንገድ፣ የውስጥ ለውስጥ ፍሳሽና መብራት ያልገባላቸው እንደሆነ፣ እንዲሁም ብዙዎቹ ሕንፃዎች ባለ18 ፎቅ በመሆናቸው አሳንሰር ያልተገጠመላቸውና እንዴት ይተላለፉ የሚለው ጥያቄ በመፍጠሩ፣ ስለሚተላፉበት ሁኔታ የዳሰሳ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን አቶ ሔኖስ ተናግረዋል፡፡

ከመሠረተ ልማት ጋር ተያይዞ ወሳኝ የሚባሉት ጉዳዮች ሳይፈቱ ቤቶቹን ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍ አሁንም የመልካም አስተዳደር ችግር ማምጣታቸው የማይቀር መሆኑ ቢታመንበትም፣ አሁን ካለው ነባራዊ  ሁኔታ አንፃር ሲታይ ቤቶቹን ለመጨረስ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማቅረብ አስቸጋሪ እንደሚሆን አክለው ተናግረዋል፡፡

በ2011 ዓ.ም. 13ኛው ዙር ዕጣ የወጣባቸው 51,229 ቤቶች በ11ኛ እና በ12ኛ ዙሮች ግንባታቸው በሚፈለገው ልክ ሳይጠናቀቅ  በችኮላ ዕጣ ወጥቶባቸው መተላለፋቸውን የገለጹት ደግሞ፣ በሚኒስቴሩ የቤቶች ልማት አገልግሎት ኃላፊ አቶ ታደሰ ከበበ ናቸው፡፡

የቤቶቹ ግንባታ በአማካይ 87 በመቶ ቢደርስም ከአምስትና ከስድስት ዓመት በፊት  ተጀምረው በግንባታ ላይ የነበሩ ናቸው ተብሏል፡፡ አብዛኞቹ ቤቶች በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ በመሆቸውና የከተማ አስተዳደሩ ከባንክ 53 ቢሊዮን ብድር የወሰደ  በመሆኑ፣ ባንኮችም ተጨማሪ ገንዘብ ለማበደር መቸገራቸውን  ተናግረዋል፡፡

ዕጣ የወጣባቸው ቤቶች በፍጥነት ለደንበኞች መተላለፍ አለባቸው የሚሉት ኃላፊው፣ አሁን ባሉበት ደረጃ ይተላለፉ የሚለው ውሳኔ በመንግሥት ከፀደቀ ለቀሪ ሥራው የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን ከቤቶቹ ዋጋ ተቀንሶ እንዲተላለፉ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ቤቶቹ አሁን ባሉበት ደረጃ ከተላለፉ ከደንበኞች የሚሰበሰበው ገንዘብ፣ የከተማ አስተዳደሩን የባንክ ብድር በተወሰነ ደረጃ ለማቅለል ይረዳል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

አየተካሄደ  ካለው የዳሰሳ ጥናት በተጨማሪ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ከፓርላማ አባላት ጋር በመሆን ተጨማሪ ዳሰሳ አካሂዶበት፣ ቤቶቹ ያሉበት ሁኔታ ለመንግሥት ማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ ቀርቦ ውሳኔ  እንደሚሰጥበት ሚኒስቴር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ከዚህ በኋላ ለዜጎች ቤት እየገነባ ማዳረስ እንደማይችልና በተለያዩ አማራጮች ማለትም 20 በመንግሥትና 80 በአልሚዎች ተሸፍኖ 20/80 በሚል አሠራር ቤቶችን ለማልማት መታሰቡን፣ ቤት ፈላጊዎችን ከአልሚዎች ጋር ለማስተሳሰር በርካታ አልሚዎችን ወደ ገበያው በማስገባት ተወዳዳሪ አድርጎ ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ቤቶች እንዲያቀርቡ እንደሚደረግ አቶ ሔኖስ ጠቁመዋል፡፡

የለማ መሬትና የፋይናንስ ችግር፣ የቴክኖሎጂ እጥረት፣ እንዲሁም ከዜጎች የመግዛት አቅም ውስንነት ጋር ተዳምሮ ቤት ማቅረብ ከባድ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በቅርቡ ይፀድቃል ተብሎ በሚጠበቀው የሪል ስቴት አዋጅ፣  አልሚዎች ተደራሽ የሆኑ ቤቶችን ለኅበረተሰቡ በስፋት ያደርሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል፡፡

በቀጣይ ቤቶች ሳይጠናቀቁ ዕጣ የማውጣት ተግባር እንዳይደገምና አሁን በሁሉም ሳይት ያሉ ቤቶች ሳይጠናቀቁ እንዳይተላለፉ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር እየተሠራ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል በክልሎች መምህራን፣ የተመለሱ የሠራዊት አባላትና የጤና ባለሙያዎች በማኅበር ተደራጅተው መሬት ቢወስዱም፣ በፋይናንስ አቅርቦት ችግር  ቤት እየገነቡ አለመሆናቸውን የገለጹት አቶ ታደሰ ናቸው፡፡
Reporter

የተሟላ፣ትኩስ እና አስተማማኝ ኮንዶሚንየም እና ሪልስቴት ነክ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.condoaddis.com/ ፌስቡክ፡- https://wwww.facebook.com/condoadis ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/CondominiumforsaleinAddisAbaba1 ቴሌግራም፦ https://t.me/condoaddis በመወዳጀት ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

የተሟላ፣ትኩስ እና አስተማማኝ ኮንዶሚንየም እና ሪልስቴት ነክ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.condoaddis.com/ ፌስቡክ፡- https://wwww.facebook.com/condoadis ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/CondominiumforsaleinAddisAbaba1
ቴሌግራም፦ https://t.me/condoaddis በመወዳጀት ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Please follow and like us:
Pin Share

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Translate »
RSS
Follow by Email
Scroll to Top