Condoaddis

የኮንዶሚኒየም ቤት ተረካቢዎች በር ለሌለው ቤት ቁልፍ ውሰዱ መባላቸውን ተናገሩ

 

የኮንዶሚኒየም ቤት ተረካቢዎች በር ለሌለው ቤት ቁልፍ ውሰዱ መባላቸውን ተናገሩ

 

የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ያልተጠናቀቀ ቤት አልሠጠሁም ብሏል

በኮዬ ፈጬ 20/80 ኮንዶሚኒየም ቤት ዕጣ የደረሳቸው ተረካቢዎች የጀርባ በሩና መስኮቱ ላልተገጠመ ቤት ቁልፍ ውሰዱ ከመባላቸውም በላይ፣ ቤቱን እንዳትቆልፉት በመባላቸው ቅሬታ እንዳደረባቸው ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መካከል ሥማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የቤት ዕድለኛ፣ ቁልፍ የሚሠጠው ሙሉ ለሙሉ ቤቶች ተጠናቀው መሆን ሲገባው፣ ምንም ዓይነት መስኮቶችና በር ሳይገጠምላቸው የቤቶቹን ቁልፍ ውስዱ ማለትየአዕምሮ ጨዋታ እየተጫወቱብንነው የሚያስብል መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።


ቅሬታ አቅራቢዎቹ ቤታችሁ ተጠናቋል ቁልፍ ውሰዱ ከተባሉ በኋላ ቤቱን ተዘዋውረው ሲመለከቱ መስኮቱ ሙሉ ለሙሉ በርም በከፊል እንዳልተገጠመለት መመልከታቸውን ተናግረዋል። ባለ ሦስት መኝታ ቤት ሠሞኑን እንደተቀበሉ የተናገሩት ቅሬታ አቅራቢ፣ ቁልፍ ከተቀበሉ በኋላ ቤታቸውን ሲጎበኙ ሦስቱም መስኮቶች እንዳልተገጠሙ ማረጋገጣቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።


አንዱ መስኮት ፍሬም ቢገጠምበትም ሌሎቹ ክፍት ናቸው የሚሉት የቤቱ ዕድለኛ፣ በኮዬ ፈጬ የሚገኘው ብሎክ 503 መስኮትና በሩ አልተገጠመም ብለዋል። ቅሬታ አቅራቢው አያይዘውም፣ ቁልፍ የሠጡን አስረክበናል ለማለት እንጅ ከዚህ በኋላ መጥተው ሊያስተካክሉልን እንደማይችሉ ከእስካሁኑ ድርጊታቸው መረዳት ይቻላል ሲሉ ነው ያብራሩት።ሌላኛው ሥሜ አይጠቀስ ያሉ ቅሬታ አቅራቢ በበኩላቸው፣ ቁልፍ ቢቀበሉም የቤታቸው በጓሮ በኩል ያለ በርና መስኮት መዝጊያ እንዳልተገጠመለት ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት። አክለውም፣ ቁልፉን ካስረከቡን በኋላ በሩ እንዲጠናቀቅላችሁ አትቆልፉት ብለውናል ያሉ ሲሆን፣ በሩ ካልተገጠመና ክፍት መሆን ካለበት ቁልፍ መቀበላችን ወደ ቤታችን ብንገባ እንኳ ንብረታችንን ለዘረፋ ቢዳርግ እንጅ ሌላ ምን ጥቅም ሊኖረው ይችላል ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል።

ይህን ጉዳይ በተመለከተም የመጀመሪያው ቅሬታ አቅራቢ በበኩላቸው፣ ቁልፍ ከተረከብን ኃላፊነትንም መውሰድ እንዳለብን አስበን ቤቱን ልንቆልፍ ስንል አትቆልፉት እንደተባሉና ለምን ብለው ሲጠይቁም ሠሞኑን እንሠራዋለን የሚል ምላሽ እንደተሠጣቸው እና በድርጊቱም ግራ እንደተጋቡ ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።የሚሰማን ሠው አጥተናልየሚሉት ቅሬታ አቅራቢው፣ በቦታው ሲዘዋወሩ ያገኟት አንዲት እናት ከቤት ብትገባም መስኮትና በር ስላልተገጠመላት በካርቶን ከልላ አግኝቻታለሁሲሉ ዕማኝነታቸውን ሠጥተዋል።

አዲስ ማለዳ ለተነሳው ቅሬታ ምላሽ ለማግኘት ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ግንባታ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ቶማስ ደበሌ ጋር ቆይታ ያደረገች ሲሆን፣ ዳይሬክተሩም ያልተጠናቀቀ ቤት እንዳልሰጡ ነው የተናገሩት።
ኮዬ ፈጬ ላይ 50 ሺሕ በላይ ቤቶች አሉ ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፣ በዚህም 1ሺሕ 71 በላይ ግንባታ እንዳለ ጠቁመው፣ ጥራት የጎደለውና ያልተጠናቀቀ ቤት ሊኖር ይችላል ሲሉ መስክረዋል። አዲስ ማለዳ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ባቀረቡት ቅሬታ መሠረት መስኮትና በር ሳይገጠም ቁልፍ መስጠት ለምን አስፈለገ ስትል ጥያቄ ያቀረበች ሲሆን፣ ቶማስም እኛ በር ሳንገጥም ቁልፍ የምንሠጠው ምንም ቤት የለም የሚል ምላሽ ሠጥተዋል።
አክለውም፣ ኮዬ ፈጨ ላይ ብሎክ 518 ኹል ጊዜ ቅሬታ እንደሚነሳበት የመሰከሩ ሲሆን፣ ገና ስላልተጠናቀቀ ቁልፍ ተረከቡ የምንልበት አቋም የለንም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ምክትል ዳይሬክተሩ አያይዘውም፣ ቁልፍ ተረክበን ቤታችን በር የለውም የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎች ለቅሬታቸው ተጨባጭ ማስረጃ ካላቸው ሒደው ማስተካከል እንደሚችሉ አመላክተዋል። ጨምረውም ቅሬታ አቅራቢዎቹ ቢሮ መጥተው ይጠይቁን ነው ያሉት።


68 ሺሕ 490 ሰዎች ቁልፍ ለመስጠት ታቅዶ፣ 42 ሺሕ በላይ ለሆኑ ሰዎች ተሠጥቷል የሚሉት ቶማስ፣ 17 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ቁልፍ እስከሚወስዱ እየጠበቁ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
አዲስ ማለዳ ቁልፍ እየተሠጠ ያለው ቤቶቹ ተጠናቀው ነው የሚል ጥያቄ ያነሳች ሲሆን፣ አዎ መጠናቀቅ የሚገባው ተጠናቋል የሚል ምላሽ ዳይሬክተሩ ሠጥተዋል


ከዚህ በፊት አዲስ ማለዳ 20/80 ቤት የደረሳቸው ሰዎች ቤታቸው ስላል ተጠናቀቀላቸውና የሚያጠናቅቁበት ብር በማጣታቸው ቤቱን በሕገ ወጥ መንገድ እየሸጡ መሆናቸውን መዘገቧ የሚታወስ ነው።

 

ምንም እንኳ መንግሥት ቤቶቹ ሳይጠናቀቁ በማስረከብ ጎደሎውን በሒደት እንደሚያሟላ መወሠኑ የሚታወስ ቢሆንም፣ ከአሁን በፊትም ሳይጠናቀቁ የተሠጡ ቤቶች መጠናቅ ባለመቻላቸው አሁንም ተመሳሳይ ድርጊት ላለመፈጸሙ ማረጋገጫ እንደሌላቸው ነው ቅሬታ አቅራቢዎቹ የገለጹት።

የተሟላ፣ትኩስ እና አስተማማኝ ኮንዶሚንየም እና ሪልስቴት ነክ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.condoaddis.com/ ፌስቡክ፡- https://wwww.facebook.com/condoadis ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/CondominiumforsaleinAddisAbaba1
ቴሌግራም፦ https://t.me/condoaddis በመወዳጀት ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Please follow and like us:
Exit mobile version