Site icon Condoaddis

የ20/80 ባለ ሶስት መኝታ ቤት ተመዝጋቢዎች በዕጣው ያልተካተቱበት ምክንያት

የ20/80 ባለ ሶስት መኝታ ቤት ተመዝጋቢዎች በእጣው ያልተካተቱት ለምንድን ነዉ?

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲያስገነባቸው የቆየዉን የ20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ የማዉጣት ስነስርዓት ትላንት አካሂዷል።
ይሁን እንጂ በ20/80 ፕሮግራም ባለ ሶስት መኝታ ቤት የ1997 ተመዝጋቢዎች በእጣዉ ያለመካተት በርካቶች ዘንድ ብዥታን የፈጠረ መሆኑን ተመልክተናል። በርካታ ስለጉዳዩ መረጃ ጠይቃችሁናል።

ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ፌስቡክ ገጽ መረዳት እንደቻለዉ በትናንት እለት እጣ ከወጣባቸዉ 25,491 ቤቶች ዉስጥ 18,648ቱ የ20/80 ፕሮግራም ቤቶች ናቸዉ። እነዚህ 18,648 ቤቶች ደግሞ ስቱድዮ፤ ባለአንድ መኝታ ቤት እና ባለሁለት መኝታ ቤት ናቸዉ።
ስለዚህም ባለ ሶስት መኝታ ቤት የ1997 ተመዝጋቢዎች በእጣዉ አልተካተቱም ማለት ነዉ።
የከተማ አስተዳደሩ “የባለ ሶስት መኝታ ቤት በተመለከተ ፕሮግራሙ ባለፈዉ ዙር በቦርድ ዉሳኔ በመዘጋቱ በቀጣይ በልዩ ሁኔታ የሚስተናገዱ ይሆናል” ሲል በፌስቡክ ገጹ ጽፏል።

የአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት የ1997ዓም 20/80 ተመዝጋቢዎች በ12ኛዉ ዙር እጣ መመሪያዉ ከሚጠይቀዉ የ60 ወር ቁጠባ ወርዶ 1500 ብር የቆጠቡት ጭምር በእጣ መካተታቸዉን ለሚዲያዎች በሰጡት ማብራሪያ ተናግረዋል።
“በ12ኛ ዙር ላይ ቦርዱ መመሪያ አስተላልፎ፤ ቃለጉባኤ ይዞ፤ ወስኖ እስከ 1500 ድረስ ወርዶ ፈቀደላቸዉ። ከዛ በኋላ ‘የመጨረሻ እስከ 1500 ወርደናል ባለ ሶስት መኝታ አልቋል’ በሚል እንዲነገር ተደረገ” ብለዋል።

ይሁን እንጂ የ20/80 ፕሮግራም ቢዘጋም ጥቂት ሰዎች የባንክ ቁጠባ አካዉንታቸዉን ሳይዘጉ መቆጠብ መቀጠላቸዉን አቶ ሽመልስ ተናግረዋል።
በትናንቱ የእጣ ስነስርዓት ያልተካተቱትም እነዚህ 20/80 ተመዝጋቢዎች ሲሆኑ ለወደፊት በሌላ መንገድ እንደሚስተናገዱም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
“አሁን አጠቃላይ ነገሩን ከምናበላሸዉና ሲስተሙንም እንደገና ከምንደበላልቀዉ ጥቂት ስለሆኑ በዚህ እጣ ዉስጥ አይካተቱ ነገር ግን ከባንክ በወሰድነዉ መረጃ መሰረት እስከ የካቲት 21 (2014) ቆጥበዉ ብቁ የሆኑትን በሌላ መንገድ እናስተናግዳቸዋለን” ብለዋል።

በድረ ገጻችን የምናቀርባቸውን መረጃዎች በአማራጭነት በቴሌግራም ቻናላችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ ይጫኑ።
👇👇👇👇👇
Https://t.me/condoaddis
እንዲሁም፦ በፌስቡክ
Https://www.fb.me/condoadis

Please follow and like us:
Exit mobile version