ዘመን ባንክ ከየት ወደ የት?

ዘመን ባንክ ከየት ወዴት?
*******
#ሪፖርተር በ ዳዊት ታዬ
👉🏼 ካፒታሉ 15 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን 7.5 ቢሊዮን የተከፈለ ካፒታል ደርሷል።
👉🏼 የደንበኞች ብዛት በ2016 ዓ.ም. መጨረሻ 222,645 ደርሷል።
👉🏼የገቢ መጠን በ2016 የሒሳብ ዓመት 7.7 ቢሊዮን ብር ደርሷል።
👉🏼የብድር መጠን በተጠናቀቀው 2016 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ 35.6 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡
********
በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለየት ባለ መንገድ አገልግሎት ለመስጠት ወደ ሥራ የገባው ዘመን ባንክ ዛሬ 16 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

ባንኩ በወቅቱ የነበረውን የባንኮች አሠራር በመፈተሽ የተሻለ ውጤት ያስገኝልኛል ብሎ ያመነውን የአንድ ቅርንጫፍ አገልግሎት ለመስጠት በመወሰን ነበር ወደ ሥራ የገባው፡፡

ወሳኝ የተባሉ የባንክ አገልግሎቶችን በአንድ ቅርንጫፍ በመስጠት ሌሎችን በዲጂታል የባንክ አገልግሎት መስጠት እንደሚችል በማመን የጀመረው ሥራ በወቅቱ እንዴት ይሆናል የሚል ጥያቄ አስነስቶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ባንኩ በአንድ ቅርንጫፍ አገልግሎት ብቻ መቀጠል አልቻለም፡፡

ትናንት መስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም. ባንኩ ደንበኞችን ለማመስገን ባዘጋጀው ፕሮግራም ላይ እንደገለጸውም እንደ አንድ ቅርንጫፍ አገልግሎትን እየሰጠ ለመቀጠል የማያስችሉ ሁኔታዎች በመፈጠራቸው እንደ ሌሎች ባንኮች ቅርንጫፎችን በመክፈት አገልግሎቱን ለማስፋት ወስኗል፡፡

የባንኩን የ16 ዓመታት ጉዞ በተመለከተ በባንኩ የተዘጋጀውን ሪፖርት ያቀረቡት የዘመን ባንክ ስትራቴጂክ ኦፊሰር አቶ ተዋህዶ ታፈሰ ዘመን ሥራ የጀመረው በአንድ ቅርንጫፍ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

‹‹ሲንግል ብራንች›› አገልግሎት ለመስጠት አልሞ የተነሳ መሆኑን የገለጹት አቶ ተዋህዶ በኋላ ግን በሁኔታዎች አስገዳጅነት በተለይም በብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመርያ ምክንያት ቅርንጫፍ የመክፈት ግዴታን በመቀበል የቅርንጫፎቹ መጠን ከፍ የማድረግ ሁኔታ ውስጥ ገብቷል፡፡

ይህም ቢሆን የቅርንጫፎችን ቁጥር ከሌሎች ባንኮች በከፍተኛ መጠን በማሳደግ ሳይሆን በተወሰነ ደረጃ ጭማሪ በማድረግ መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡

አቶ ተዋህዶ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ ‹‹ይህ የቅርንጫፍ ቁጥር ባንኩ ላለው ከፍተኛ አፈጻጸም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፤›› ብለዋል፡፡

ይህም የባንኩ ጠቅላላ ትርፍ በእያንዳንዱ ቅርንጫፍና ሠራተኛ ቁጥር ሲመዘን ባንኩ በኢንዱስትሪው ውስጥ በጥቂት ቅርንጫፎችና የሠራተኛ ቁጥር ከፍተኛ ትርፍ በማስገኘት በቀዳሚነት እንዲቀመጥ አድርጎታል፡፡

ባንኩ 1,830 ሠራተኞች ብቻ ያለው ሲሆን ይህ ቁጥር ካስገኘው የትርፍ አንፃር ሲመዘን በኢንዱስትሪው ቀዳሚውን ደረጃ እንዲይዝ አስችሎታል፡፡

ዘመን ባንክ ሥራ በጀመረበት የመጀመርያው ዓመት ያሰባሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 278 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ነገር ግን በመጀመርያው አሥር ዓመት ውስጥ በአማካይ አንድ ቢሊዮን ብር እያሳደገ መጥቷል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2018 በኋላ ግን በዓመት በአማካይ 5.5 ቢሊዮን ብር እያደገ ቀሪዎችን ስድስት ዓመታት ስለመጓዙ ተጠቅሷል፡፡

የመጨረሻዎች ስድስት ዓመታት ፈጣን በሚባል ጉዞ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን እያሳደገ መምጣቱም በ2016 የሒሳብ ዓመት አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ብቻ ሳይሆን የብድር አቅርቦቱን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ችሏል፡፡

ባንኩ ሥራ በጀመረበት የመጀመርያው ዓመት ለደንበኞቹ ሰጥቶ የነበረው የብድር መጠን 185 ሚሊዮን ብር ብቻ ነበር፡፡ ይህ የብድር መጠን በተጠናቀቀው 2016 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ 35.6 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

የብድር አቅርቦት ዕድገቱን በተመለከተ ከተሰጠው ማብራሪያ መረዳት የሚቻለው በመጀመርያዎቹ አሥር ዓመት በአማካይ 480 ሚሊዮን ብር ዕድገት እያሳየ ሊጓዝ የነበረ መሆኑ ነው፡፡

በመጨረሻዎቹ ስድስት ዓመት ግን ባንኩ የሰጠው የብድር መጠን በዓመት አምስት ቢሊዮን ብር ዕድገት እያሳየ አሁን ያለበት ደረጃ ሊደርስ ችሏል፡፡ በባንኩ የ16 ዓመታት ጉዞ ከፍተኛ ዕድገት የታየበት አፈጻጸም ነበር ተብሎ የተጠቀሰው ሌላው ክዋኔ በውጭ ምንዛሪ ግኝት ተገኘ የተባለው ውጤት ነው፡፡

በዚህ ረገድ ባንኩ ካገኘው ውጤት በኢንዱስትሪው ውስጥ በከፍተኛነቱ የሚጠቀሰው መሆኑም ተገልጿል፡፡

ባንኩ ወደ ሥራ በገባበት ዓመት 93 ሚሊዮን ዶላር አግኝቶ የነበረ ሲሆን፣ ይህ የውጭ ምንዛሪ በየዓመቱ እያደገ በመሄድ ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ ሊደርስ መቻሉ ተጠቅሷል፡፡

የ2010 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይም የባንኩ የውጭ ምንዛሪ ዓመታዊ ግኝት 566 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡

ዘመን ባንክ አሁን የደረሰበት ዓመታዊ የውጭ ምንዛሪ ግኝት በኢንዱስትሪው ውስጥ ሦስተኛው ከፍተኛው የውጭ ምንዛሪ ግኝት ስለመሆኑም ከተሰጠው ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

ባንኩ ከፍተኛ ዕድገት እያሳየበት የመጣው ሌላው ክዋኔው የዓመታዊ ገቢው መጠን ነው፡፡

በዕለቱ በቀረበው ሪፖርትም ዘመን ባንክ ከ16 ዓመት በፊት የመጀመርያው ዓመት የተመዘገበው ገቢ 18 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው፡፡ ይህ የገቢ መጠን በ2016 የሒሳብ ዓመት 7.7 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ እንደ ሌሎች አፈጻጸሞቹ ዓመታዊ ገቢው በመጀመርያዎቹ አሥር ዓመታት አማካይ ዕድገቱ 100 ሚሊዮን ብር ነው፡፡

ባለፉት ስድስት ዓመታት ግን ዓመታዊ የገቢ ምጣኔው በዓመት 1.1 ቢሊዮን ብር እያደገ መጥቷል፡፡

እንዲህ ያሉ የባንኩ አፈጻጸሞች የባንኩን የተከታታይ ዓመታት የትርፍ መጠን በተመሳሳይ እያሳደጉት መጥተዋል፡፡

በዕለቱ በቀረበው ሪፖርትም የባንኩ አጠቃላይ ትርፍ (ግሮስ ፕሮፊት) በመጀመርያዎቹ አምስት ዓመታት አማካይ 36.8 ሚሊዮን ብር ዕድገት ያሳየ ሲሆን፣ በመጨረሻዎቹ ስድስት ዓመታት ደግሞ በአማካይ የ596 ሚሊዮን ብር ትርፍ አግኝቷል፡፡ በ2016 መጨረሻ ላይ ደግሞ ዓመታዊ ትርፉ 3.9 ቢሊዮን ብር ሊደርስ ችሏል፡፡ ባንኩ ወደ ሥራ በገባበት የመጀመርያ ዓመት 1,395 ደንበኞች ብቻ የነበሩት ሲሆን ይህ ቁጥር በ2016 ዓ.ም. መጨረሻ 222,645 ደርሷል፡፡

ባንኩ ከዲጂታል የባንክ አገልግሎት አንፃር ቀድሞ በመንቀሳቀስ የሚጠቀስ ሲሆን አሁንም የዲጂታል የባንክ አገልግሎቱን በማስፋት እየሠራ ነው፡፡

ይህም በአሁኑ ወቅት በዲጂታል መንገድ የተንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን 66.9 በመቶ መድረሱ ማሳያ ነው ተብሏል፡፡

ባንኩ ከዓመት ዓመት በሁሉም የባንክ ሥራ አገልግሎት መመዘኛዎች እያስመዘገበ ያለውን ዕድገትና የፋይናንስ አቅሙን የበለጠ ለማጠንከር የተለያዩ ዕርምጃዎች እየወሰደ ይገኛል፡፡ እንደ ማሳያ የገለጹትም የባንኩን ካፒታል ለማሳደግ የወሰደውን ዕርምጃ ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ ረገድ እስከ ሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ የተፈረመ ካፒታሉ 15 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የተከፈለ ካፒታሉ ደግሞ 7.5 ቢሊዮን ብር መድረስ ችሏል፡፡
#ዘመንባንክ #ZemenBank #Banking #stockmarket #Ethiopia

 

Please follow and like us:
Pin Share

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Translate »
RSS
Follow by Email
Scroll to Top