በማኅበር ቤት ለመገንባት የተመዘገቡ መረጃቸው በአጭር ጊዜ ተጣርቶ ሊደራጁ ነው።

በማኅበር ቤት ለመገንባት የተመዘገቡ መረጃቸው በአጭር ጊዜ ተጣርቶ ሊደራጁ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ በመጋቢት ወር 2013 ዓ.ም. በማኅበር ተደራጅተው የጋራ መኖሪያ ቤት ለመገንባት እንዲችሉ የመዘገባቸው 12,611 ተመዝጋቢዎች፣ መረጃቸው ተጣርቶ በአጭር ጊዜ እንደሚደራጁና ቀሪ ሥራዎች እንደሚጀመሩ አስታወቀ፡፡

.

ቢሮው ከዚህ በፊት በበይነ መረብ የመዘገባቸው የማኅበር ቤት ፈላጊዎች እስከ መጋቢት 16 ቀን 2014 ዓ.ም. በሚኖሩበት ክፍላተ ከተማ ቀርበው፣ ከዚህ ቀደም የቤት ባለቤት ወይም የቤት ባለዕድል አለመሆናቸውን የሚገልጽ ማስረጃ እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርቧል፡፡

.

የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ በመጋቢት 2013 ዓ.ም. የቁጠባ ክፍያቸውን ያላቋረጡ የ2005 ዓ.ም. የ40/60 ተመዝጋቢዎች፣ በማኅበር ተደራጅተው የጋራ መኖሪያ ቤት ለመሥራት እንዲችሉ የሚያደርግ መመርያ አዘጋጅቶ፣ 12,611 ተመዝጋቢዎችን በበይነ መረብ መመዝገቡ ይታወሳል፡፡

.

ከዚህ ቀደም በአማራጩ የተመዘገቡ ተመዝጋቢዎችን የማደራጀት ሥራ ከ14ኛው ዙር የጋራ ቤቶች ዕጣ ማውጣት በኋላ እንደሚከናወን ሲገለጽ ቢቆይም፣ ተግባራዊ ሳይደረግ ቆይቷል፡፡

.

የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ የቤት ልማት ትግበራና የሥራ ዕድል ፈጠራ ክትትልና ቁጥጥር ዋና ዳይሬክተር ኪያ በሬቻ (ኢንጂነር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አማራጩ በተቀመጠለት አቅጣጫ እንዳይሄድ ካደረጉት ጉዳዮች ውስጥ የመሬት ዝግጅት ጉዳይ ተጠቃሹ ነው፡፡ ለፕሮጀክቱ በጠቅላላው 50 ሔክታር መሬት ያስፈልግ እንደነበር ያስረዱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በአንድ በኩል መሀል ከተማ ላይ ይህንን ያህል ስፋት ያለው መሬት ማግኘት፣ በሌላ በኩል መሬቱ ሲገኝም ጥልቅ የወሰን ማስከበር ሥራዎችን ማከናወን ጊዜ ወስዷል ብለዋል፡፡

.

የማኅበር ቤት አማራጭ ሲተገበር 70 በመቶ በቅድሚያ ክፍያ፣ 30 በመቶ ባንኮች አማካይነት ተመቻችቶ ነው፡፡ ‹‹ከባንኮቹ ጋር የሚደረገው ዝግጀት ከተጠናቀቀ የቆየ ቢሆንም የመሬት ዝግጀቱ ቶሎ አለመጠናቀቁ ማነቆ ሆኖ ቆይቷል›› ያሉት ኪያ (ኢንጂነር)፣ የማደራጀቱ ሥራ ጊዜ የጠየቀው የመሬት ዝግጅት ሳይጠናቀቅ ቢደረግ ሊፈጥር የሚችለውን ችግር ታሳቢ በማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

.

በቀጣይ የመረጃ ማጥራት ሥራው ሲጠናቀቅ ማኅበራቱን የማደራጀት ሥራ እንደሚጀመር የተገለጸ ሲሆን፣ ማኅበራቱ በዕጣ አማካይነት በተለያዩ ሳይቶች ይደራጃሉ ተብሏል፡፡ ዕጣ ለማውጣት የሚያገለግለው ሶፍትዌር ከተዘጋጀ ሦስት ወራት እንደሆነው ተገልጾ፣ ከማጣራቱ በኋላ ዕጣውን የማውጣት ሥራ እንደሚከናወን ተጠቁሟል፡፡ ከዚያም በማኅበራት የማደራጀት ሥራው እንደተጠናቀቅ፣ በቀጥታ ወደ ግንባታ እንደሚገባ ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

የቤት ልማት ትግበራ ዋና ዳይሬክተሩ እንዳስረዱት፣ ለዚህ አማራጭ የተመዘገቡት ዜጎች መረጃ መልሶ በሚጣራበት ጊዜ ተመዝጋቢዎች ቤት ያላቸው ናቸው ወይስ አይደሉም? በትዳር አጋሮቻቸው ስም ቤት ያላቸውንና የሌላቸው የሚሉትን መረጃዎች በሚገባ ይፈተናሉ፡፡ በዚህ ወቅት ተመዝጋቢዎቹ ባሉበት ወረዳና ክፍላተ ከተማ ቅጽ እየሞሉ መረጃቸው በመጣራት ላይ ነው ብለዋል፡፡

ለማኅበር ቤት ግንባታ አማራጭ አስፈላጊ የሆነው የመሬት ዝግጅትና የዲዛይን ሥራ የተጠናቀቀ መሆኑን፣ በመጀመሪያው ዙር ብቻ የተመዘገቡት 12,611 ተመዝጋቢዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል፡፡                                                                                          

የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮው በከተማዋ ያለው የቤት ፍላጎት በመንግሥት አስተናባሪነት ብቻ የሚሸፈን ባለመሆኑ፣ የግል ዘርፉ በቤት ልማት እንዲሳተፍ የሚያስችል የተለያዩ የቤት ልማት አማራጮችን እያየ መሆኑ ከዚህ ቀደም መግለጹ ይታወሳል፡፡

ከዚህ ውስጥ አንደኛው የሆነው የኪራይ ቤት አማራጭ ግንባታ ሲሆን፣ በዚህ አማራጭ በ2012 ዓ.ም. የ440 ቤቶች ግንባታ ተጀምሮ በፋይናንስና በሌሎች ችግሮች ሳቢያ ቆሞ ነበር፡፡ የተቋረጠውን ግንባታ የማስቀጠሉ ሥራ የተጀመረ መሆኑን፣ በተጨማሪም በዚህ ዓመት ይህንን አማራጭ ለማስፋት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ቢሮው አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን አማካይነት እንዲገነቡ በቅርቡ ሥራቸው የተጀመሩት የተገጣጣሚ ቤቶች ግንባታ ከጅማሮ ግንባታው በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፣ በመንግሥትና የግል አጋርነት የቤት ልማት አማራጭም የቤት ልማት ለማከናወን የቻይናው ኩባንያ ሲሲኢሲሲ የአዋጭነት ጥናት እያከናወነ መሆኑን ኪያ (ኢንጂነር) አስታውቀዋል፡፡

 ሪፖርተር

የተሟላ፣ትኩስ እና አስተማማኝ ኮንዶሚንየም እና ሪልስቴት ነክ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.condoaddis.com/ ፌስቡክ፡- https://wwww.facebook.com/condoadis ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/CondominiumforsaleinAddisAbaba1
ቴሌግራም፦ https://t.me/condoaddis በመወዳጀት ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Please follow and like us:
Pin Share

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Translate »
RSS
Follow by Email
Scroll to Top