ቢጂአይ ኢትዮጵያ በሕገወጥ ሰነድ የባለቤትነትን ድርሻ አሳጥቷል በሚል ክስ ተመሠረተበት

  • ለ23 ዓመታት ያልተከፈለ የትርፍ ድርሻ ከእነ ወለዱ ተሠልቶ እንዲከፈል የዳኝነት ጥያቄ ቀርቧል

በ1983 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካን የ‹‹ካስቴል ግሩፕ›› ዋና ባለድርሻ ለሆኑት ሚስተር ካስትል ሲሸጥ፣ 27 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ኢትዮጵያዊ የሆኑት ወ/ሮ ዘውድነሽ ጌታሁን የተባሉ ባለሀብት የገዙ ቢሆንም፣ ባላወቁት ሁኔታ በሕገወጥ መንገድና በሐሰተኛ ሰነድ ድርሻቸውን ለሌላ ግለሰብ በማስተላለፍ እንደተነጠቁ በማብራራት፣ በቢጂአይ ኢትዮጵያና ሌሎች ሦስት ተከሳሾች ላይ ክስ መሠረቱ፡፡

ከሳሽ በጠበቆቻቸው አማካይነት ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ንግድና ኢንቨስትመንት ጉዳዮች ልዩ ችሎት ግንቦት 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ባቀረቡት ክስ እንዳብራሩት፣ በልጃቸው አማካይነት ከ‹‹ካስቴል ግሩፕ›› ባለቤት ጋር በመሆን የቢጂአይ ኢትዮጵያን ድርጅት 9,450 አክሲዮን ወይም 23 በመቶ ድርሻ ገዝተዋል፡፡ ጥር 29 ቀን 1988 ዓ.ም. የካስቴል ግሩፕ አካል ከሆነው ‹‹ሶሼቴ ዴ ብራሴሪ ኤት ግለሴር ኢንተርናሽናል›› በምኅፃረ ቃል ቢጂአይ (Societe Des Brasseries et Glaciers Internationals –BGI) ጋር በመሆን ድርጅቱን መሥርተዋል፡፡

‹‹የድርጅቱ 27 በመቶ ድርሻ በኢትዮጵያኖች መሆን አለበት›› በመባሉ፣ ድርሻው መሻሻል ስለነበረበት መጋቢት 17 ቀን 1988 ዓ.ም. በተደረገ ልዩ ጠቅላላ ጉባዔ የነበራቸው ድርሻ (አክሲዮን) ወደ 11,651 (27 በመቶ) ከፍ መደረጉም በክሱ ተገልጿል፡፡

ድርጅቱ በወቅቱ ሊያመርት ባሰበው ቢራ፣ ወይን ጠጅና ጋዝ ያላቸው ምርቶች፣ ማምረቻ ቦታዎችን በልጃቸው በኩል በማፈላለግ ባቲ ኮምቦልቻ ሰፊ ቦታ ተረክበው፣ የባቲ ቢራን በማምረት ድርጅቱ ወደ ሥራ መግባቱን አብራራርተዋል፡፡

በአዋጅ ቁጥር 87/1986 የተቋቋመው የኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራን ወደ ግል ለማዛወር ያወጣውን ጨረታ ‹‹ብራስሪየስ ሆልዲንግ ሊሚትድ›› የተባለው የ‹‹ካስቴል ግሩፕ›› አባል ድርጅት ጨረታውን በ10 ሚሊዮን ዶላር ማሸነፉ ይታወሳል፡፡

ከሳሽ ወ/ሮ ዘውድነሽ 27 በመቶ ድርሻቸውን ይዘው የአክሲዮን ድርሻ ድልድል ተደርጎ ሚያዝያ 11 ቀን 1993 ዓ.ም. በተሻሻለ መመሥረቻ ጽሑፍ በውልና ማስረጃ መፅደቁንና መፈረማቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡

ድርጅቱ ከዓመት ዓመት ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ቢሆንም፣ 27 በመቶ ድርሻቸው በሕግና በማስረጃ የተረጋገጠ ሆኖ ሳለ፣ በድርጅቱ ያላቸውን ድርሻ ሙሉ በሙሉ እንዳስተላለፉ በማስመሰል በሐሰተኛ ሰነድ የተደገፈ ሕገወጥ ተግባር እንደተፈጸመባቸውና ድርሻቸው ለሌላ አካል መተላለፉ በክሱ ተብራርቷል፡፡

ተከሳሾቹ ቢጂአይ ኢትዮጵያ፣ ሚስተር ዤን ፖል ብላቪር፣ ብራስሪየስ ኢንተርናሽነናል ሆልዲንግ ሊሚትድ (ቢአይኤች) እና ህቡ ፕሮፐርቲስ ሊሚትድ ሲሆኑ፣ ከሳሽ በቢጂአይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያላቸውን ድርሻ ለብራስሪየስ ኢንተርናሽናል ሆልዲንግ ሊሚትድና ለህቡ ፕሮፐርቲስ ሊሚትድ ሕገወጥ በሆነ መንገድ ተላልፎ እንዲሰጥ ማደረጉን ክሱ ያብራራል፡፡

ይህ የሆነው ደግሞ በወቅቱ በኢትዮጵያ ተፈጥሮ በነበረው የፖለቲካ መከፋፈልን ምክንያት በማድረግ፣ ድርሻቸውን ለመንጠቅ መሆኑንም ክሱ ያብራራል፡፡

በወቅቱ ከነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን ባለቤት የነበሩት የሕወሓት አመራሮች መካከል በነበረው የፖለቲካ መሰነጣጠቅ ምክንያት፣ መንግሥት ‹‹‹በሙስና ጠርጥሬአቸዋለሁ›› ያላቸውን እነ አቶ ሥዬ አብርሃን ጨምሮ ወንድማቸውን የኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ የቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት አቶ አሰፋ አብርሃ ሲከሰሱ፣ ከክሳቸው መካከል አንዱ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ ጨረታ ጋር የተያያዘ እንደነበር በክሱ አስታውሰዋል፡፡

ልጃቸው በወቅቱ ከአቶ ሥዬና ከአቶ አሰፋ ጋር ጥብቅ ግንኙነት የነበራት በመሆኑ፣ የፖለቲካ ጎራ እንዳላት በማድረግና ጫና በማሳረፍ ከአገር እንድትወጣ መደረጉን የገለጹት ከሳሽ ወ/ሮ ዘውድነሽ፣ እሳቸውንም በማስፈራራት ከአካባቢው እንዲርቁ በማድረግ፣ በወቅቱ የቢጂአይ ኢትዮጵያ የሕግ ክፍል ሠራተኛ የነበሩትና አሁንም ከአንድ በመቶ በታች ድርሻ ያላቸው አቶ ሐጎስ በደሱ ዋናውን ሚና እንደተጫወቱ ገልጸዋል፡፡

ከሳሽም በወቅቱ ለሕይወታቸው በመፍራትና የተሻለ ጊዜ እስኪመጣ በማለት፣ ላለፉት 23 ዓመታት የትርፍ ድርሻም ይሁን ድርጅቱ ምን ላይ እንዳለ ሳይጠይቁ መቆየታቸውን በክሱ በሰፊው አብራርተዋል፡፡

ከ2010 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ በኋላ ስትሮክ ታመው ግማሽ ፓራላይዝ በመሆናቸውና ከፍተኛ የጤና ችግር ገጥሟቸው በመክረማቸው፣ የደረሰባቸውን በደል ለሕግ ሳያቀርቡ መቆየታቸውን አብራርተው፣ በቅርቡ ድርጅቱ ቢጂአይ ኢትዮጵያ ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ ለሚባል ድርጅት መሸጡን ቤተሰቦቻቸው ሲነግሯቸው፣ መብታቸው ለሦስተኛ ወገን ሳይተላለፍ የሕግ ጥያቄ ማንሳታቸውንም በክሱ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ከሚያዝያ 11 ቀን 1993 ዓ.ም. ጀምሮ 27 በመቶ ድርሻቸው ፀድቆ የፈረሙ በመሆኑ፣ የአክሲዮን ድርሻቸው የወ/ሮ ዘውድነሽ ጌታሁን ነው ተብሎ እንዲወሰንላቸው፣ ላለፉት 23 ዓመታት ምንም ዓይነት የትርፍ ክፍያ ያላገኙ በመሆኑ በዋና ኦዲተር ተጣርቶና መጠኑ ታውቆ በድርሻቸው ልክ ከሕጋዊ ወለድ ጋር ታስቦ እንዲከፈላቸውና ሁሉም ተከሳሾች በሐሰተኛ ሰነድ ድርሻቸውን ለሌላ አካል በማዛወራቸው፣ በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር የወንጀል ምርመራ እንዲደረግ፣ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡

ከሪፖርተር

Please follow and like us:
Pin Share

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Translate »
RSS
Follow by Email
Scroll to Top